የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀሰን መሐመድ ከጃፓን ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (JICA) ልዑክ አባላት ጋር ተወያዩ

ታህሳስ 7/2018 ዓ.ም (ኢሚ) የኢፌዴሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የመሰረተ ልማትና ግብዓት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀሰን መሐመድ ቀጣይነት ያለው የቢዝነስ ዲቨሎፕመንት አገልግሎት ፕሮጀክት ላይ ከጃፓን ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (JICA) ልዑክ አባላት ጋር ተወያይተዋል፡፡

አቶ ሀሰን መሐመድ ሀገራችን የኢኮኖሚ እድገት እና ልማትን ለማረጋገጥ በምታደርገው ጉዞ JICA የኢንዱስትሪ እድገት የጀርባ አጥንት የሆነውን ጥቃቅን፣ አነስተኛና እና መካከለኛ አምራች ድርጅቶችን ጠንካራ፣ የረዥም ጊዜና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው ብለዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም ሴቶች እና ወጣቶች በጥቃቅን አነስተኛ እና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች የስራ እድል እንዲፈጠርላቸውና የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራው ባለው ስራ የጃፓን ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (JICA) እያደረገ ላለው ትብብር እና አጋርነት አመስግነው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ለቀጣይ 3 አመታት የሚተገበረውን የቢዝነስ ዲቨሎፕመንት ኢኒሸቲቭ ለማሳካት ከአጋር የፌዴራል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንዲሁም ከሌሎች ተቋማት ጋር በትብብር እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

በጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (JICA) የቢዝነስ ዲቨሎመንት ፕሮጀት ሌደር ኮዮኮ ሳንዳባታክ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ከታህሳስ 2025 እኤአ አስከ ታህሳስ 2028 እኤአ ለሶስት ዓመታት የሚተገበር ይሆናል ብለዋል፡፡

Share this Post