በ2018 በጀት ዓመት ባለፉት አስራ አንድ ወራት ከአምራች ኢንዱስትሪዉ ዘርፍ በወጪ ንግድ የተሻለ አፈጻጸም ተመዘገበ
ሰኔ 2/2018ዓ.ም (ኢ.ሚ)የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በ2018 በጀት ዓመት ያለፉት አስራ አንድ ወራት የአምራች ኢንዱስትሪውን የወጪ ንግድ አፈጻጸም የገመገመ ሲሆን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ አፈጻጸም ማሳየቱን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ገልጸዋል።
ባለፉት 11 ወራት የጨርቃጨርቅና አልባሳት፤ የምግብና መጠጥ ዘርፍ ፤የቆዳና ቆዳ ውጤቶች እና የኬሚካልና የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ወደ ተለያዩ ሃገራት ተልከው ከ2017 ዓ.ም የስራ ዘመን ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ አፈጻጸም እንዳለው በግምገማው ተገልጻል፡፡
አቶ መላኩ አክለውም ባለፉት 11 ወራት ዘርፉ የተለያዩ አለም አቀፋዊ ተግዳሮቶችን አልፎ ያሰመዘገባቸውን ስኬቶች አድንቀው በተናጥል ሲታይ የወጭ ንግድ አፈጻጸማቸው ዝቅ ያለባቸው ኢንዱስትሪዎች በማህበራቸው አማካኝነት ጥልቅ ውይይት በማድረግ የኤክስፖርት አፈጻጸማቸውን ማሳደግ ላይ መስራት እንዳለባቸው አሳስበው መስሪያቤቱ አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚያገጥሟቸውን ችግሮች እየተከታተለ እንደሚፈታም ገልጸዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ በበኩላቸው አምራች ኢንዱስትሪዎች በተለያዩ ምክንያቶች ኤክስፖርት ሳያደረጉ ያከማቿቸውን ምርቶች ባጠረ ጊዜ ኤክስፖርት በማድረግ ሀገሪቱ ማግኘት ያለባትን የውጭ ምንዛሬ ግኝት ማስገኘት ላይ አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ አሳስበዋል፡፡
በአፈጻጸም ግምገማው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ፣ የተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ባለሙያዎች እና የአምራች ኢንዱስትሪ ባለቤቶች የተገኙ ሲሆን የ2018 በጀት ዓመት ያለፉት አስራ አንድ ወራት የወጪ ንግድ አፈጻጸም ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።