ሲሚንቶ የማምረት አቅማችንን ከአየር ንብረት ተጠያቂነት ጋር የማጣጣም ስራ እየተሰራ ነው
ሀምሌ 1/2018 ዓ.ም (ኢሚ) በኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ትብብር አዘጋጅነት The Africa Dialogue on Cement for Green Industrialization" የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄ ነው።
የኢፌዴሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በመድረኩ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር የአምራች ኢንዱስትሪዎቻችንን የማምረት አቅም ከአየር ንብረት ተጠያቂነት ጋር የማጣጣም ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው ከአምራች ኢንዱስትሪዎች መካከል አንዱ የሆነውን የሲሚንቶ ፍብሪካ እንደ ማሳያ በማንሳት የሲሚንቶን አስፈላጊነት እና ለአፍሪካ ልማት ያለውን ወሳኝ ሚና አንስተዋል ።
ሚኒስትሩ ሲሚንቶ ማለት በጣም አስፈላጊ የሆነ እና ህልማችንን ወደ እውነታ የምንቀይርበት ቁስ ነው" ይሁን እንጂ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች የተጨማሪ ሲሚንቶ ግብዓቶችን እና አማራጭ የኃይል ምንጮችን ለመጠቀም እየተደረገ ያለው የሙከራ ሂደት ሲሚንቶን ወደ አረንጓዴ ኢንዱስትሪ መለወጥ ህልም ሳይሆን እውን መሆኑን የሚያሳይ ነውም ብለዋል፡፡
ሚኒስትሩ አክለውም አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ሰለባ ከመሆን ወጥታ፣ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የአረንጓዴ ልማት መፍትሄ አመንጪ መሆኗን የምታሳይበት ታላቅ መድረክ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (UNIDO) የአፍሪካ ህብረት እና የኢኮኖሚ ኮሚሽን (UN ECA) ተወካይ ክልላዊ ቢሮ ዳይሬክተር ስቴፋን ካርቦ (Stefan Kargbo) በሚኒስትሩ የቀረበውን ሀሳብ በመደገፍ የሲሚንቶ ኢንዱስትሪ ያለውን የአየር ንብረት ተጽዕኖ በስፋት አብራርተዋል፡፡
ዳይሬክተሩ እንደገለጹት፣ ሲሚንቶ ለአፍሪካ ልማት የጀርባ አጥንት ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ትልቁ የአየር ንብረት ለውጥ ፈተና መቀጠሉን ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት ካለው መረጃ አንጻር ሲሚንቶ እንደ አንድ ሀገር ቢቆጠር ኖሮ በዓለም ላይ ሦስተኛው ትልቁ የካርቦን ዳይኦክሳይድ በካይ ጋዝ አመንጪ ይሆን ነበር ብለዋል።
የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (UNIDO) አባል ሀገራት የካርቦን ልቀትን የቀነሰ የሲሚንቶ ምርት (Low-carbon cement) እንዲያመርቱ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የአማራጭ ነዳጅ አጠቃቀም እና የደረጃዎች ማውጣት ስራዎችን እየደገፈ እንደሚገኝ የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ለአብነት የምትጠቀስ ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።
ቀጥለውም ካርግቦ ሲገልፁ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2025 የቤሌም መግለጫን (Belém Declaration) በማጽደቅ ከፍተኛ ልቀት ያላቸውን የኢንዱስትሪ ዘርፎች ለመቀነስ ቁርጠኝነቷን ያሳየች ሲሆን፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ሲሚንቶ አምራቾች ማህበር ጋር በመሆን የአማራጭ ኃይል አጠቃቀም ላይ ሰፊ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል ሲሉ ገልፀዋል ። ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በአዲስ አበባ አቅራቢያ የሚገኘው የሀበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካ የተጨማሪ ሲሚንቶ ግብዓቶችን እና አማራጭ የኃይል ምንጮችን ለመጠቀም እያደረገ ያለው የሙከራ ሂደት ሲሚንቶን ወደ አረንጓዴ ኢንዱስትሪ መለወጥ ህልም ሳይሆን እውን መሆኑን ያሳየበት ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡
የውይይት መድረኩ ከሰኔ 30 2018 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን ዛሬ ሐምሌ 1 ቀን 2018 ዓ.ም የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡ በስብሰባው የተለያዩ የአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት አመራሮች፣ ባለሙያዎች እና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡