የኢንዱስትሪ ፓርኩ መገንባት መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት በተጨባጭ ያረጋገጠ ነው
የኢንዱስትሪ ፓርኩ መገንባት መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት በተጨባጭ ያረጋገጠ ነው
የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ መገንባት መንግሥት የኢንዱስትሪው ዘርፍ ለሀገር ያለውን አበርክቶ ለማሳደግ በፖሊሲና በስትራቴጂ ከመደገፍ ባለፈ በተጨባጭ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየበት መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ለኢዜአ ገለጹ።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ባሳለፍነው ሳምንት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቆ የተከፈተውን የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጎብኝተዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ መገንባት፤ መንግሥት የኢንዱስትሪው ዘርፍ ለሀገር ያለውን አበርክቶ ለማሳደግ በፖሊሲና በስትራቴጂ ከመደገፍ ባለፈ በተጨባጭ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየበት ነው።
ፓርኩ በአምራች ዘርፉ ላይ የሚስተዋለውን የመሥሪያ ቦታ እጥረት በዘላቂነት ለመፍታት የማይተካካ ሚና አለው ብለዋል።
አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች አቅማቸውን ገንብተው ወደ ከፍተኛ ኢንዱስትሪነት እንዲሸጋገሩ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
ፓርኩ የተገነባበት ጥራትና የተሟላ መሠረተ ልማት የሀገር ውስጥ ምርትን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ ያስችላል ሲሉም ገልፀዋል።
የሀገር ውስጥ ምርትን በማሳደግ የገቢ ምርቶችን ለመተካት የሚደረገውን ጥረት ለሀገር ዘላቂ ሉዓላዊነት ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንዲህ አይነት ግዙፍ ፕሮጀክት መገንባቱ ትልቅ ልምድና ትምህርት የተገኘበት መሆኑን ጠቅሰው፤ ለሌሎች አካባቢዎችም እንደ ማዕከልና አርዓያ ሆኖ እንደሚያገለግል አስገንዝበዋል።
በሁሉም አካባቢዎች ኢንዱስትሪን ለማስፋፋትና የሀገርን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ጉልህ ሚና ይጫወታልም ብለዋል።