ሀሴት የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማምረቻ ፋብሪካ በቅርብ ምርቱን ለሀገር ውስጥ ገበያ ያቀርባል
ሰኔ 09/2018 ዓ.ም (ኢሚ) ለምርትና ምርታማነት ትልቅ ድርሻ ያለውን የአፈር ማዳበሪያ በሀገር ውስጥ በማማምረት ለሀገር ውስጥ ገበያ ለማቅረብ ዝግጅቱን በማጠናቀቅ ላይ የሚገኘውን ሀሴት የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማምረቻ ፋብሪካ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ጎብኝተዋል።
የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማምረት ወደ ሀገር ውስጥ ገበያ ለማስገባት በሂደት ላይ ያለውን ፋብሪካ የአመራረት ሂደት እና የምርት ጥራት የተመለከቱት ሚኒስትሩ ሀገራችን ከያዘችው በርካታ ወጪ የሚወጣበትን ሰው ሰራሽ የአፈር ማዳበሪያ በተፈጥሮ የአፈር ማዳበሪያ ለመተካት እንደ ሀገር እየተሰራ ያለውን ስራ ሊያግዝ የሚችል መሆኑን ተናግረዋል ፡፡
በተለይም በሀገራችን መመረቱ የማዳበሪያ አቅርቦትና ስርጭት በወቅቱና በሰዓቱ በሚፈለገው መጠን ለአርሶና ከፊል አርብቶ አደሩ ተደራሽ እንዲሆን ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ያሉት ሚኒስትሩ የአፈርን ለምነት በመጠበቅ ታክሞ ለረጅም ጊዜ ለምነቱን እንዲጠብቅ እና የምርት ጥራት በመጨመር ከፍተኛ ምርት እንዲገኝ የሚያስችል ማዳበሪያ መሆኑን ገልፀዋል።
በቀጣይም ምርቱን በስፋት በማምረትና በማስተዋወቅ ለገበያ ተደረሽ እንዲሆን መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ሀሴት የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማምረቻ ስራ አስኪያጅ አቶ ሄኖክ ስሞን በበኩላቸው የተፈጥሮ ማዳበሪያ በግብርና ሚኒስቴር ላቦራቶሪ እና በኢትዮጵያ ደረጃዎች ተቋም ጥራቱን የማረጋገጥ ስራዎች ተጠናቀዋል ብለዋል ፡፡
ፍብሪካው ውጤታማነቱን በማረጋገጡ በቅርብ ምርቱን ለሀገር ውስጥ ገበያ ለማቅረብ ዝግጅት ያጠናቀቅ ሲሆን በቀን መቶ ሺህ በላይ ኪሎ ግራም ማዳበሪያ በማምረት ለ85 ሰዎች ቋሚ የስራ ዕድል መፍጠሩን አስረድተዋል ፡፡