አምራች ኢንዱስትሪ ለአንድ ሀገር የምርት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የህልውናም ጉዳይ ነው፡፡
መጋቢት 30/2018 ዓ.ም (ኢሚ) የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል የኢትዮጵያ የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ዘጠነኛ ጠቅላላ ጉባኤ የማስጀመሪያ መርሃ - ግብር ላይ እንደገለፁት የምናመርተው ምርት በሀገር ውስጥ ገበያም ሆነ በውጭ ገበያ ሲሸጥ በጥራት እና በዋጋ አቅርቦት እንዲሁም በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን አለበት።
ሚኒስትሩ የአምራች ዘርፉን በማሳደግ ሂደት ዉስጥ በሀገራዊ ኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ ሊኖረው የሚገባውን ጉልህ ሚና ይበልጥ ለማጠናከር እና በዓለም አቀፍ ገበያ ተፈላጊ እና የምርቶቻችን ተፈላጊነት እንዲጨምር ጠንካራ ሀገር አቀፍ የአምራች ምክር ቤት ያስፈልገናል ሲሉ ገልፀዋል ፡፡
በእያንዳንዱ ኢንዱስትሪ የሚመጣው ሀገራዊ ዕድገት ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ነው ፣ በማህበር የመደራጀትን አስፈላጊነትን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በማመን ብዙ ስራዎች ሲሰራ መቆየቱን ገልጸው እናንተ አምራቾች ከመንግስት ጋር ለመናበብ ተግባብቶ ለመስራት እንዲሁም የአምራች ኢንዱስትሪ ባለቤቶች የመደራደር አቅም ከፍ ለማድረግ በማህበር መደራጀት ያለዉን ጠቀሜታ ገልጸው የሀገር አቀፍ የዘርፍ ማህበራት ም/ቤትም ለዚህ ወሳኝ ሚና አለዉ ብለዋል።
በዓለም ላይ የአምራች ኢንዱስትሪ ማህበራት ረዥም ታሪክ ያለው በመሆኑ ከኛ ከቀደሙ እና በዘርፉ ውጤታማ ከሆኑ ሀገሮች ልምድ ለመቅሰም እና ተጠቃሚ ለመሆን በማህበር መደራጀት አይነተኛው መንገድ ነው ሲሉ ገልፀዋል ፡፡
የዳይሬክተሮች ቦርድ ምርጫ ሃገራዊ በሆነ ስሜት ምክር ቤቱን ወደ ከፍተኛ ደረጃ ያሻግራሉ ተብሎ የሚታመኑ እና ከመንግስት ጋር አምራች ኢንዱስትሪውን በማቀራረብ እርስ በእርስ ልምድና ተሞክሮ በመለዋወጥ ጤናማ የውድድር ስርዓት በመዘርጋት ሀገራችን ከአምራች ኢንዱስትሪው ተጠቃሚና ተወዳዳሪ ሆና የምወጣበትን ስራ እንዲሰሩ መልክዕክት አስተላልፈዋል ።
ነባሩ የአምራች ዘርፍ ምክር ቤት እስካሁን ለሰራው ስራ አመስግነዉ ከአዲሱም ተመራጮች ጋራ በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸዉን አንስተው የጀመርነውን ምቹ የአምራች ኢንዱስትሪ ፖሊሲ አጠናክረን በመቀጠል ለአምራች ኢንዱስትሪው እናደርጋለንም ብለዋል።
በአገር አቀፍ የዘርፍ ማህበራት ም/ቤት በተደረገዉ ምርጫ አቶ ጀማል አህመድ እና አቶ በላይነህ ክንዴ ፕሬዚዳንት እና ም/ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል ።