ትራንስፎርመር አምራች ኢንዱስትሪዎች የሀገር ውስጥ ገበያን ለማርካት ስትራቴጅክ እቅድ ይዘው መስራት አለባቸው (አቶ ሀሰን መሐመድ )
መጋቢት 8/2018 ዓ.ም (ኢ.ሚ)የኢፌዴሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከኤሌክትሪክ ቁሳቁስ አምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር የውይይት መድረክ አካሄደ፡፡
የውይይት መድረኩን የመሩት የኢንዱስትሪ መሰረተ ልማትና ግብዓት ዘርፍ ሚንስትር ዴኤታ አቶ ሀሰን መሐመድ ትራንስፎርመር አምራች ኢንዱስትሪዎች አሁን ላይ ያለውን የሀገር ውስጥ የገበያ ፍላጎትን ታሳቢ በማድረግ በተመጣጣኝ ዋጋ ለተጠቃሚዎች ምርታቸውን የሚያቀርቡበትን ሁኔታ ለመፍጠር ስትራቴጅክ ዕቅድ አውጥተው መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
ዘርፉ ከ2010 ዓ.ም ወዲህ ከውጭ ጥሬ እቃዎችን እያመጣ ከመገጣጠም ተነስቶ አሁን ላይ ራሱን ችሎ በተወሰነ ደረጃ ማምረት መቻሉ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ያመጣው ለውጥ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሀሰን ዘርፉን ለማጠናከር የማበረታቻ ስርዓትን በተመለከተ ኢንዱስትሪ ሚንስቴር ከኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ጋር እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ተሳታፊ አምራች ኢንዱስትሪዎች በበኩላቸው መንግስት ያመቻቸላቸውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው የማምረት አቅማቸውን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደጉ እንደመጡና ቀደም ሲል ተበላሽተው የወደቁ ትራንስፎርመሮችን በመጠገን እንደገና ጥቅም ላይ እንዲውሉ አድርገው ለተጠቃሚ እያቀረቡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የመርሀ ግብሩ ዋና ዓላማ በዘርፉ የተሰማሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች እርስ በእርሳቸው የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ ለማስቻል ሲሆን በውይይቱ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪ አገልግሎትና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል ፡፡