የአንድ ሀገር ጥንካሬ የሚለካው ወደ ሌላው ዓለም አምርታ በምትልከው ምርት መጠን ነው(አቶ መላኩ አለበል)

መጋቢት1/2018 ዓ.ም(ኢ.ሚ)የኢፌዴሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የስምንት ወራት የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ኤክስፖርት አፈፃፀምን በተመለከተ ከአምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር የግምገማ መድረክ አካሄደ፡፡

የግምገማ መድረኩን የመሩት የኢንዱስትሪ ሚንስትር አቶ መላኩ አለበል የአንድ ሀገር ጥንካሬ የሚለካው ወደ ሌላ ዓለም አምርታ በምትልከው የምርት መጠን እንደሆነ ገልጸው አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ መድረስ ያለበትን የዕድገት ደረጃ እንዲደርስ የኤክስፖርት አቅም ቀጣይነት ባለው ሁኔታ እየጨመረ መሄድ እንጅ በተለያየ ጊዜ ከፍና ዝቅ የሚል አፈፃፀም መኖር የለበትም ብለዋል፡፡

ሚንስትሩ ሁሉም አምራች ኢንዱስትሪ በተመሳሳይ ደረጃ ጥሩ የኤክስፖርት አቅም እንዲኖረው እያንዳንዱ አምራች ኢንዱስትሪ አስተዳደራዊ መዋቅሩን ተፈትሾ በትክክለኛው መንገድ መመራት አለበት ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች የሚፈጥሩትን ኢ-ተገማች ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ መንግስት ልዩ ዲፕሎማሲያዊ አካሄዶችን ተጠቅሞ ለመፍታት አበክሮ እየሰራ ስለሆነ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ሁሉም አምራች ኢንዱስትሪ ዓመታዊ የኤክስፖርት ዕቅዱን ማሳካት አለበት ሲሉ አሳስበዋል፡፡

በመርሀ ግብሩ በ2018 በጀት ዓመት የስምንት ወራት የኤክስፖርት አፈፃፀም 289.2 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሬ መገኘቱ የተገለጸ ሲሆን እንደ ሀገር በስምንት ወራት 300 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ከታቀደው ዕቅድ አንፃር አፈፃፀሙን 96% አድርሶታል፡፡

ይህም ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተመዘገው አፈፃፀም ጋር ሲነፃፀር በዚህ ዓመት ያለው የኤክስፖርት አቅም የ 41% ዕድገት አሳይቷል፡፡

Share this Post