መንግስት የግል ዘርፉን ያነቃቁ በርካታ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል። አቶ መላኩ አለበል
የካቲት 10/2018 ዓ.ም (ኢሚ) የ2018 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ የማስጀመሪያ መርሃግብር ላይ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግስት የኢኮኖሚያዊ ለውጥ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የግል ዘርፉን ያነቃቁ በርካታ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል ።
በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙም ሆነ በ10 አመቱ የልማት ዕቅድ ውስጥ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራባቸው ከሚገኙ የኢኮኖሚ መስኮች ውስጥ አንዱ የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ነው ብለዋል ።
ዘርፉ ከራሱ ባህሪ ከሚመነጩ ተግዳሮቶች ባሻገር ሰፊ ከአመለካከት፣ ከፖሊሲ፣ ከህግ ማዕቀፎች እና ከመንግስታዊ አገልግሎት አሰጣጦች በሚመነጩ ማነቆዎች እና ስር በሰደዱ ስርዓታዊ ችግሮች ሲፈተን መቆየቱን ያነሱት አቶ መላኩ በዚሁ የተነሳም አጠቃላይ የዘርፉ የማምረት አቅም አጠቃቀም 50 በመቶ በታች ወርዶ ነበር ብለዋል።
የዘርፉን ማነቆና ችግሮች በስትራቴጂካዊ ብልሀት እና በፍጥነት እየፈቱ መሄድ የውዴታ ሳይሆን የሞት የሽረት ጉዳይ መሆኑን በመንግስት ቁርጠኛ አቋም መወሰዱን ተናግረዋል ።
በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት የማምረት አቅም አጠቃቀም በ2014 ከነበረበት 46 ከመቶ ወደ 66.3 ከመቶ ማሳደግ መቻሉን ገልፀዋል ።