ኢትዮጵያ ወደ ኢንዱስትራላይዜሽን ለመሸጋገር ለምታደርገው ጥረት የኢንዱስትሪ ካውንስሉ ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ (አምባሳደር ግርማ ብሩ)
የአምራች ኢንዱስትሪ ብሔራዊ ካውንስል በ2018 በጀት ዓመት የ6 ወር ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ገምግሟል፡፡
የካውንስሉ የ6ወር ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በተገመገመበት ወቅት የካውንስሉ ሰብሳቢ አምባሳደር ግርማ ብሩ እደንገለጹት ካውንስሉ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን እያስቀመጠ በመሆኑ በዘርፉ የለውጥ ዕድገት መኖሩን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ወደ ኢንዱስትራላይዜሽን ለመሸጋገር ለምታደርገው ጥረት ጣልቃ ገብነት በማስፈለጉ የተቋቋመው አምራች ኢንዱስትሪ ብሔራዊ ካውንስሉ በዘርፉ ከፍተኛ ተፅዕኖ ሊያመጡ የሚችሉትን ኢንዱስትሪዎች መነሻ በማድረግ ያለባቸውን ዋና ዋና ማነቆዎችን በመለየት ችግሮቹን ለመፍታት የሚያስችሉ በየ15 ቀኑ በመወያየት አቅጣጫዎችን እያስቀመጠ ለአፈፃፀማቸው ክትትልና ግማገማ እያደረገ በመሆኑ አበረታች የሆኑ ውጤቶች መምጣታቸውን አምባሳደር ግርማ ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም የማምረት አቅም አጠቃቀም፣ ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት፣ ምርቶችን ወደ ውጪ በመላክ የተገኘ የውጪ ምንዛሬ እና የተፈጠረ ተጨማሪ የስራ ዕድል በዘርፉ ዕድገትና የተሻለ አፈጻጻም ከታየባቸው መካከል እንደሆኑ አምባሳደር ጠቅሰዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው አምራች ኢንዱስትሪ ብሔራዊ ካውንስል ተቋቁሞ ወደ ስራ ከገባ ጀምሮ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ያሉበትን የስራ እንቅስቃሴ በመስክ ምልከታ የድጋፍና ክትትል በመደረጉ በዘርፍ መነቃቃትን የፈጠረ፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ቅንጅታዊ አሰራር የተዘረጋበት እንዲሁም ዘርፉ ትኩረት እንዲያገኝ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡
የጥጥ ምርት፣ የጥሬ ቆዳና ሌጦ ልማትና የግብይት ስርዓት ተግዳሮት ግብይትና አማራጭን በተመለከተ ለካውንስሉ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡