የበለጸገች አገር የምትገነባው በበለጸገ ዜጋ ነው(አቶ መላኩ አለበል)
ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣በንግድና ቀጠናዊ ሚኒስቴርና በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ቅንጅታዊ አሰራር ጨውን በአዮዲንና በፎሊክ አሲድ የሚያበለጽግ የምርምር ውጤት ይፋ ሆነ፡፡
የምርምር ውጤቱን ለማስተዋወቅ በተዘጋጀው መድረክ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢንዱስትሪ ሚንስትር አቶ መላኩ አለበል የበለጸገች ሀገር የምትገነባው በበለጸገ ዜጋ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አቶ መላኩ አንድ ዜጋ ሁለንተናዊ ብልጽግና ሊኖረው የሚችለው በአስፈላጊ ማዕድናት የበለጸገ ምግብና ጥራት ያለው ትምህርት ማግኘት ሲችል እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
የፈጠራ ውጤቱ የህጻናትን የመቀንጨር ችግር በዘላቂነት ይፈታል ያሉት ሚንስትሩ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ ወዲህ አምራች ኢንዱስትሪው እያደገ በመምጣቱ ምክንያት ሌሎች ዘርፎችም ተያይዘው ዕድገት አሳይተዋል፡፡
ለዚህም የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ ጨውን በአዮዲንና በፎሊክ አሲድ ለማበልጸግ ያስቻለው ውጤታማ የምርምር ስራ መሰራቱ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
ሚንስትሩ በቀጣይም በምርምር ውጤቱ ህብረተሰቡ በፍትሀዊነት ተጠቃሚ እንዲሆን በቂ የግብዓት አቅርቦት፣ በሁሉም ምርቱን በሚያመርቱ ፋብሪካዎች ተመሳሳይ የጥራት ደረጃ እንዲኖርና አምራች ኢንዱስትሪዎች ምርቱን ለማምረት አስፈላጊ ቴክኖሎጅዎችን ማሟላት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
ለፕሮጀክቱ መሳካት የራሳቸውን ሚና ለተጫወቱ ባለድርሻ አካላት ሚኒስትሩ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ሀይሉ በበኩላቸው የጨቅላ ህፃናትን ሞትና የዕድሜ ልክ የአካል ጉዳትን የሚያመጣ የነርብ ዘንግ ክፍተት ችግርን ለመቅረፍ ባለፉት ስድስት ዓመታት ጨውን በአዮዲንና በፎሊክ አሲድ ለማበልጸግ ለሚደረገው ምርምር ላበረከቱት አስተዋጽኦ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን አመስግነዋል፡፡