በአምራች ኢንዱስትሪ ምርታማነት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል (አቶ ሀሰን መሃመድ )
ታህሳስ 27/2018 ዓ.ም (ኢሚ) የኢፌዴሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በኢንተርፕራይዞች የደረጃ ሽግግር መመሪያ እና የምርምር፣ የቴክኖሎጅ ልማትና ሽግግር ፍኖተ ካርታ ላይ ለኢንዱስትሪና ማዕድን ቋሚ ኮሚቴ አመራርና አባላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በሰጠበት ወቅት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የመሠረተ ልማትና ግብዓት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀሰን መሃመድ እንደገለፁት የሀገራችንን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማፋጠን እና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ፣ የዜጎችን የኑሮ ደረጃን ለማሻሻል አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን ማሳደግ ምርጫ የሌለው ጉዳይ በመሆኑ ዘርፉ ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች አንዱና ቀዳሚው ነው።
የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ በባህሪው ውስጣዊና በዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶች፣ ማነቆዎች እና ተጽዕኖ አሳዳሪ ሁኔታዎች ጭምር የሚፈትኑት መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሀሰን የዘርፉን ሀገራዊ አቅም በማሳደግ ተወዳዳሪነቱን ለማረጋገጥ ካሰብን ተግዳሮቶቹና ማነቆዎቹን ለመፍታት የምንሄድበት ርቀት እና ጉዳዮቹን የምንመለከትበት መነጽር የተለየ መሆን እንዳለበት ገልፀዋል፡፡
የአምራች ኢንዱስትሪ ካውንስሉና የኢንዱስትሪና ማዕድን ቋሚ ኮሚቴው ክትትልና ድጋፍ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍን ለማነቃቃት በተደረጉ ጥረቶች መዋቅራዊ ችግሩን ለመፍታት በፖሊሲና ስትራቴጂ በርካታ ተግባራት ተፈፃሚ በመሆናቸው በማምረት አቅም አጠቃቀም፣ በወጪ ምርት ለውጦች እየመጡ ከመሆኑም በላይ በተኪ ምርቶች አመርቂ ውጤት በዘርፉ እየተመዘገበ ይገኛልያሉት ሚኒስትር ዴኤታው በዘርፉ እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶች ለማስጠበቅና ዘላቂነታቸውን ለማረጋገጥ እንዲሁም ወደፊት ሊመጡ የሚችሉ የዘርፉ ፈተናዎችን ቀድሞ በመተንበይ ዝግጁ ለመሆን በርካታ ባለድርሻ አካላትን አቀናጅቶ መስራትን ይጠይቃል ብለዋል።
የአምራች ኢንዱስትሪ ምርታማነት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የሁሉንም ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑ ግልፅ ነውያሉት አቶ ሀሰን አቅም የሚሆኑ የተዘጋጁ ስትራቴጂዎችን በየደረጃው ግንዛቤ በመፍጠር በተሟላ መንገድ ወደ ትግበራ እንዲገቡ ለማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናው መዘጋጀቱን ገልፀዋል ።
የኢንዱስትሪና ማዕድን ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ ፈቃዱ መንግስቱ (ዶ/ር) በበኩላቸው የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ተስፋ ሰጭ መሆናቸውን ጠቁመው እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ይበልጥ አጠናክሮ በመቀጠል ዘርፉ የተጣለበትን ሀገራዊ ኃላፊነት እንዲወጣ ለማስቻል ቋሚ ኮሚቴው ድጋፍና ክትትሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል ።
ከቋሚ ኮሚቴ አመራርና አባላት የሚሰጡ የማስተካከያ አስተያየቶችና ተጨማሪ የማዳበሪያ ሀሳቦች መመሪያው እና ፍኖተ ካርታው ዳብሮና ማስተካከያ ተደርጎበት ወደ ስራ የሚገባ ይሆናል።