ከለውጡ በኋላ በአማራ ክልል ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ በመግባት በከፍተኛ ሁኔታ ውጤታማ እየሆኑ መጥተዋል( አቶ መላኩ አለበል)

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪና የአምራች ኢንዱስትሪ ብሔራዊ ካውንስል ሰብሳቢ አምባሳደር ግርማ ብሩ፣ የግብርና ሚኒስትሩ አዲሱ አረጋ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ፣ የጉሙሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ እና ከፍተኛ የመንግስት አመራር አባላት በአማራ ክልል በደብረ ብርሃን ከተማ ዙሪያ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን ጎበኙ።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ከለውጡ በኋላ በአማራ ክልል ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ በመግባት በከፍተኛ ሁኔታ ውጤታማ እየሆኑ መጥተዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ መግባታቸውን ጠቅሰው ተጨማሪ አዳዲስ ፋብሪካዎችም ሥራ ለመጀመር ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን አስታውቀዋል።

ታህሳስ 14/2018 ዓ.ም (ኢሚ) የነባር ኢንዱስትሪዎችም የማምረት አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን አመልክተው፤ አዲሶቹ ደግሞ ስትራቴጂካዊ ምርቶችን የሚያመርቱ መሆናቸውን አመልክተው ስትራቴጂካዊ ምርቶችን የሚያመርቱ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች በስፋት ወደ ሥራ መግባታቸው ገልጸዋል ።

‎የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ በበኩላቸው፤ መንግስት የኢንዱስትሪ ዘርፉ ውጤታማ እንዲሆን በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን ተናግረዋል።  ይህንንም ተከትሎ በሀገሪቱ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ተስፋ ሰጪ ውጤት እያስመዘገቡ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

‎በደብረ ብርሃንና በዙሪያዋ የሚገኙ ከተሞች በኢንዱስትሪው ዘርፍ እያከናወኑት ያለው ተግባር ውጤታማ መሆኑን መመልከታቸውን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።  ኢንዱስትሪዎቹ የሀገሪቱን ገቢ በማሳደግ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ ያሉት ሚኒስትሯ፤ ለዘርፉ በቂ ድጋፍ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በቀጣይም ከገቢ አሰባሰብ ጋር ተያይዞ ከኢንዱስትሪ ባለቤቶች ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።  ‎የደብረ ብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት በበኩላቸው፤ በከተማው ያለውን ምቹ የኢንዱስትሪ ሁኔታ ተከትሎ በርካታ ፋብሪካዎች እየተገነቡ መሆኑን ገልጸዋል።  በበጀት ዓመቱ ጥቂት ወራትም 14 አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ በመግባታቸው ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን አስታውቀዋል።  ከንቲባው በከተማው የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ሌሎች ባለሀብቶችም በኢንዱስትሪ ዘርፍ እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል።  ጉብኝትም የደብረ ብርሃንን የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ ይበልጥ የማነቃቃትና ውጤታማ የማድረግ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

Share this Post