በአምራች ኢንዱስትሪዎች የሚነሱ ጥያቄዎችን በጋራ መፍታት ለሀገር ዕድገት ቁልፍ መፍትሄ ነው(አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ)

ታህሳስ15/2018 ዓ.ም (ኢ.ሚ) የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የዕድገትና ተወዳዳሪነት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ አዲሱን የገቢ ግብር አዋጅ ማሻሻያ እና ተያያዥ የታክስ ጉዳዮችን በተመለከተ ከአምራች ኢንዱስትሪ ማህበራት ለሚነሱ ጥያቄዎች ግልጽነትን ለመፍጠር እና በዘርፉ የሚያግጥሙ ተግዳሮቶችን ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ውይይት አካሂደዋል፡፡

አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ በሃገራችን የኢኮኖሚ እድገት የሚኖረውን ሚና በማሰብ መንግስት የሃገር ውስጥ ምርትን የሚያበረታታ ግልጽ አቅጣጫ የሰጠ ሲሆን የሚወጡ የታክስ እና ሌሎች ህጎችም ለአምራች ኢንዱስትሪው ልዩ ትኩረትን የሰጠ ፣ ህግን ተከትሎ የሚሰራና የሚያበረታታ ነው ብለዋል፡፡

ከሌሎች ተቋማት ጋር የሚደረጉ ውይይቶች የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማሳድግ ውጤት እያመጡ ስለሆነ አጠናክሮ መቀጠል ተገቢ እንደሆነ የገለፁት ሚኒስትር ዴኤታው በውይይቱ ተሳታፊ ተቋማት በአምራች ኢንዱስትሪዎች የተነሱ ጥያቄዎችን በጋራ መፍታት ለሀገር ዕድገት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት አምኖ መስራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡

በውይይቱ የግምሩክ ኮሚሽን፣ የገቢዎች ሚኒስቴር እና የገንዘብ ሚኒስቴር ተወካዮች የተገኙ ሲሆን አምራች ኢንዱስትሪው ያለበትን ቁመናና ያጋጠሙ ችግሮችን የተመለከተ ለውይይቱ የሚሆን መነሻ ጹሁፍ በአምራች ኢንዱስትሪ ማህበራት ተወካዮች ቀርቦ በተሳታፊዎች ጥያቄዎች ተነስተው በሚመለከታቸው ተቋማት ምላሽ እና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

Share this Post