ለዘላቂ የአምራች ኢንዱስትሪ ዕድገት የተሰጠው ትኩረት ተጨባጭ ውጤት እያመጣ ነው /አምባሳደር ግርማ ብሩ/
ለዘላቂ የአምራች ኢንዱስትሪ ዕድገት አስቻይ ሁኔታዎችን በመፍጠርና ቅንጅታዊ አሠራርን በማጠናከር ተጨባጭ ውጤት መገኘቱን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪና የአምራች ኢንዱስትሪ ብሔራዊ ካውንስል ሰብሳቢ አምባሳደር ግርማ ብሩ ገለጹ።
የመደመር መንግሥት ለኢንዱስትሪያዊነት ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠርና በቅንጅት በመሥራት ዘላቂና ውጤታማ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ዕድገት ማምጣት ላይ ትኩረት ማድረጉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጻፉት የመደመር መንግሥት መፅሐፋቸው ገልጸዋል።
በዚህ ረገድ መንግሥት ለኢንዱስትሪዎች ዕድገት በዋናነት የመሠረተ ልማት ግንባታ፣ የሰው ኃይል ልማት፣ አገልግሎትን ማዘመን፣ ግብዓትና ትሥሥር፣ የፖሊሲና የሕግ አስቻይ ሁኔታዎችን እየፈጠረ መሆኑም እንዲሁ።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የአምራች ኢንዱስትሪ ብሔራዊ ካውንስል አባላት ዛሬ በባህር ዳር ከተማ በሚገኙ የተለያዩ የብረታ ብረት፣ የጨርቃጨርቅ እና የአግሮ ኢንዱስትሪ ፋብሪካዎች የመስክ ምልከታ አድርገዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪና የአምራች ኢንዱስትሪ ብሔራዊ ካውንስል ሰብሳቢ አምባሳደር ግርማ ብሩ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ መንግሥት የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ነባራዊ ሁኔታ በመቃኘት እያጋጠሙ ለሚገኙ ችግሮች በቅንጅት መፍትሔ እየሰጠ ይገኛል።
ካውንስሉ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ተጨባጭ ሁኔታ በመስክ ምልከታ በመገምገም፣ በዘርፉ የሚታዩ ማነቆዎችን በቅንጅት በመፍታት፣ ፋብሪካዎች ይበልጥ እንዲጠናከሩና ውጤታማ እንዲሆኑ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡
የጉብኝቱ ዓላማ ኢንዱስትሪዎቹ ያሉበትን ነባራዊ ሁኔታ በመቃኘት እያጋጠሙ ለሚገኙ ችግሮች በቅንጅት መፍትሔ መስጠት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በባህር ዳር የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች የሀገር ውስጥ ምርትን በመተካት እና ከግብርና ዘርፍ ጋር ጠንካራ ትስስር በመፍጠር ተጨባጭ ውጤት እያሳዩ መሆኑን የካውንስሉ አባለት መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡
ለዘላቂ የአምራች ኢንዱስትሪ ዕድገት አስቻይ ሁኔታዎችን ከመፍጠር ባለፈ ቅንጅታዊ አሠራር መጠናከሩ ለዘርፉ ዕድገት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።
ካውንስሉ ከባለሀብቶች የሚቀርቡለትን መዋቅራዊ ችግሮች በመፍታት ዘርፉ በኢኮኖሚው ላይ የሚኖረውን ድርሻ ለማሳደግ እንደሚሰራም አምባሳደሩ አረጋግጠዋል።