በዘመናዊ የግብይት ስርዓት ያልተደገፈ አምራች ኢንዱስትሪ ውጤታማ አይሆንም(አቶ መላኩ አለበል)

ህዳር 22/2018 ዓ.ም ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከኢትዮ ቴሌ ኮም ጋር በመተባበር ያዘጋጀውን አምራች ኢንዱስትሪዎችን እርስ በእርስ የሚያስተሳስር የኢትዮጵያ ታምርት የመገበያያ ፕላት ፎርም (Be to Be E commerce Plat form) የማስጀመሪያ ወርክ ሾፕ ተካሄደ፡፡ 

በመርሀ ግብሩ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በዘመናዊ የግብይት ስርዓት ያልተደገፈ አምራች ኢንዱስትሪ ውጤታማ አይሆንም ሲሉ ገልጸዋል፡፡  አቶ መላኩ የአምራች ኢንዱስትሪዎች ግብይት ከዘመኑ ጋር አብሮ መሄድ ስላለበት በዲጅታል ፕላትፎርም የታገዘ ግብይት መጀመሩ ለዘርፉ ዕድገት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ሲሉ አብራርተዋል፡፡  የዘመነ የግብይት ስርዓት ለአምራች ኢንዱስትሪው አስፈላጊ ነዉ ያሉት አቶ መላኩ የኢትዮጵያ አምራች ኢንዱስትሪዎችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሩ አዲሱ የዲጅታል ግብይት ፕላትፎርም በዘርፉ ውስጥ የገቡ አላስፈላጊ ተዋናዮችን በመቆጣጠር ዜጎች ከአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ በፍትሀዊነት ተጠቃሚ እንዲሆኑና አምራቾች ያመረቱትን ምርት ለማን፣መቼና እንዴት መሸጥ እንዳለባቸው እንደሚያስችል አስገንዝበዋል፡፡

የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የእርስበርስ የገበያ ትስስርን የሚያሳልጠው አዲሱ የኢትዮጵያ ታምርት የዲጅታል ግብይት ፕላትፎርም ሀገር በቀል ምርቶች የሀገር ውስጥን ፍላጎት አርክተው ወደ አፍሪካ ገበያ እንዲገቡ ከማድረግ ባሻገር ከሌሎች ፕላትፎርሞች በተለየ መልኩ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ የሚከታተለው እንደ መሆኑ መጠን ዜጎችን ከአጭበርባሪዎች እንደሚታደግና የዘርፉን በርካታ ችግሮች እንደሚፈታ ገልጸዋል፡፡

ከፕላትፎርም ትግበራ በኋላ አምራች ኢንዱስትሪዎችንና ተጠቃሚ ግለሰቦችን የሚያስተሳስር ፕላትፎርም ደግሞ እንደሚለማ ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም ሁሉም አምራች ኢንዱስትሪዎች በፈቃደኝነት ትኩረት ሰጥተው አዲሱን የኢትዮጵያ ታምርት ፕላትፎርም እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ቺፍ የኢንተርፕራይዝ ኦፊሰር አቶ ዮሀንስ ጌታሁን በበኩላቸው ፕላትፎርሙ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች አስፈላጊና ወሳኝ የሆኑ የሰው ሰራሽ አስተውሎት መተግበሪያዎችን ያካተተ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በመርሀ ግብሩ የኢትዮ ቴሌኮም የስራ ሀላፊዎችን ጨምሮ የተለያዩ የአምራች ኢንዱስትሪ ተወካዮችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን ወርክ ሾፑ እስከ ህዳር 24/2018 ዓ.ም ድረስ ይቀጥላል፡፡

Share this Post