ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ሐዋሳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ውስጥ የሚገኘውን ቶዮ ሶላር ጎበኙ

ነሐሴ 9/2017 ዓ.ም (ኢ.ሚ) የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በሐዋሳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ውስጥ የሚገኘውን ቶዮ ሶላር ዛሬ ጎብኝተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሐዋሳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን በነበራቸው ጉብኝት ቶዮ ሶላር ከፀሐይ ብርሃን ኃይል ማመንጨት የሚያስችሉ ሶላር ፓናሎችን እያመረተ በመመልከታቸው ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

በጉብኝቱ የሶላር ፋብሪካው ከፍተኛ ጥራት ያለው ምርት የማምረት አቅም የተላበሰ እና ዘመናዊ የምርት ሥርዓት እንደሚከተል መታዘባቸውን ጠቁመው ኩባኒያው ምርቱን ወደ ወጪ ሀገራት በመላክ ለሀገሪቱ ውጪ ንግድ እድገት አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ያላቸውን ተስፋ አመላክተዋል።

የኩባኒያው ሥራ እሴት የተጨመረባቸው ምርቶች ለዓለም ገበያ በማቅረብ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ያስቀመጠቻቸውን የአምራች ኢንዱስትሪ ግቦች እና ፖሊሲዎች ከሚያሳኩ ጨዋታ ቀያሪ ፕሮጀክቶች አንዱ መሆኑን ያመላከቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) ስራው ከመንግስት የኢንቨስትመንት ስትራቴጂያችን ጋር የተጣጣመ መሆኑንም አስምረውበታል።

ከዚህ ቀደም ቬይትናም የሚገኘውን የቶዮ ሶላር ፋብሪካ በጎበኙበት ወቅት ከኩባንያው ፕሬዝደንቱ ጋር በነበራቸው ውይይት የፀሐይ ብርሃን ኃይል ማመንጫዎችን በኢትዮጵያ ለማምረት ተስማምተው እንደነበር አስታውሰዋል።

ቶዮ ሶላር የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በሚያስተዳድረው ሐዋሳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ውስጥ 110 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ገደማ የሚገመት ሀብት በሁለት ምዕራፍ ስራ ላይ በማዋል ከአንድ ሺህ ለሚበልጡ ኢትዮጵያውያን የስራ ዕድል መፍጠሩ ይታወቃል፡፡

#ኢትዮጵያ_ታምርት

#እኛም_እንሸምት

Share this Post