የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪ ምርታማነትን እያሳደገ ነው - አቶ መላኩ አለበል
የካቲት 19/2018 ዓ.ም(ኢሚ) የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ዣንጥራር አባይ እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በአዲስ አበባ በሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች የሥራ ጉብኝት አድርገዋል።
የጉብኝቱ ዓላማ የ"ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ ያስገኛቸውን ውጤቶች ለመገምገም እና በአምራቾች ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመለየት ነው።
አቶ መላኩ አለበል በዚሁ ወቅት፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ግብ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን አቅም ማሳደግና በኤክስፖርት ላይ የተሰማሩትን ለመደገፍ ያለመ ነው ብለዋል፡፡
በዚህ ረገድ ንቅናቄው የኤክስፖርት ገቢን በመጨመርና የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት ረገድ ከፍተኛ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደደር ምክትል ከንቲባ አቶ ዣንጥራር አባይ፤ በአዲስ አበባ የማምረት አቅም አጠቃቀም 69.9 በመቶ መድረሱን ጠቅሰው፤ አስተዳደሩ የማምረቻ ቦታዎችን በማመቻቸትና የገበያ ትስስር ችግሮችን በመፍታት ድጋፉን እያጠናከረ መሆኑን አብራርተዋል።
አምራቾች በበኩላቸው፤ ንቅናቄው ምርቶቻቸውን በስፋት ለገበያ እንዲያቀርቡ፣ ምርታማነታቸው እንዲጨምርና ሰፊ የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ እያገዛቸው መሆኑን ገልጸዋል።