ያልተመጣጠነ ምግብ በህብረተሰቡ ላይ ከሚያስከትለው የጤና ችግር በተጨማሪ ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት እንቅፋት ነው (አቶ መላኩ አለበል ኢንዱስትሪ ሚኒስትር)
ነሐሴ25/2016ዓ.ም (ኢ.ሚ)በሀገር አቀፍ ደረጃ ብሔራዊ የምግብ ማበልፀግ ፕሮግራም እና የ5 አመት ስትራቴጂክ እቅድ ማስተዋወቂያ መድረክ ተካሄዷል። በማስተዋወቂያ መርሃ ግብሩ መንግስት የአምራች ኢንዱስትሪውን ችግሮች ለመፍታት ሁሉን አቀፍ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተግባራዊ የማድረግ እና አስፈላጊውን የህግ ማእቀፎችን አውጥቶ ተግባራዊ በማድረግ ጅምር ውጤቶች መምጣት መጀመራቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ገልፀዋል። ከአመጋጋብ ጋር የሚመጡ የጤና ችግሮችን ለመቀነስ ብሎም ለማጥፋት ተግባራዊ ከተደረጉ ስራዎች መካከል የምግብ ማበልፀግ ፕሮግራም አንዱ ነው ያሉት አቶ መላኩ በህብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ተደራሽነት ባላቸው የምግብ ጨው እ.ኤ.አ በ2011 እና በ2022 በምግብ ዘይት እና ስንዴ ዱቄት ምርቶች ላይ እንደተጀመረ ገልፀዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ፕሮግራሙን ውጤታማ ለማድረግ ከጤና ሚኒስቴርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እንዲሁም አጋር ድርጅቶች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የበለፀገ ምርትን ለህብረተሰቡ ለማቅረብ በአምራች ኢንዱስትሪዎች የተጀመሩ ስራዎች ቢኖሩም ከአስገዳጅ ደረጃዎች አተገባባር አንፃር ክፍተቶች አሉ ያሉት አቶ መላኩ ችግሩን ለመቅረፍም ፕሮግራሙን እና ለማስፈፀሚያነት የወጡ አስገዳጅ ደረጃዎችን ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ ጠቁመዋል። ምርታማና በአቅሙ የዳበረ ተወዳዳሪ አምራች ዜጋ ለማፍራትና ምርትና ምርታማነት በማሳደግ እድገት ለማምጣት በንጥረ ነገር የበለፀገ ምግብ ለዜጎች ወሳኝ ነው ያሉት ሚኒስትሩ በአገር ደረጃ የተጀመረው የሌማት ትሩፋት አካል የሆነውን ይህን ፕሮግራም በአምራች ኢንዱስትሪ ውጤታማ ለማድረግ በርካታ ማበረታቻዎች ተቀርፀው ወደ ስራ ለመግባት ዝግጅት ላይ መሆኑንም ገልፀዋል። ለፕሮግራሙ ውጤታማነትና ለዕቅዱ መሳካት የሁሉንም ባለድርሻ አካላትና ቅንጅትና የአጋር ድርጅቶች ድጋፍ ወሳኝነት እንዳለው ግልፀዋል።