ባለፉት አምስት ዓመታት የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ተነሳሽነት ከእይታ ወደ እውነታነት ተሻሽሏል።
መስከረም 21/2018 ዓ.ም ((ኢሚ) የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (UNIDO) ምክትል ተወካይ አቶ አሰግድ መብራቱ በጣሊያ የልማት ትብብር ኤጀንሲ (AICS) የሚደገፈው የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪያል ፓርኮች ፕሮጀክት ኦፕሬሽንና ዘላቂነት ሶስተኛው የፌዴራል የፕሮጀክት አስተባባሪ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ እንደገለፁት ባለፉት አምስት ዓመታት የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪያል ፓርኮች ተነሳሽነት ከእይታ ወደ እውነታነት ተሻሽሏል።
ሶስቱ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እያንዳንዳቸው በየራሳቸው የገጠር ትራንስፎርሜሽን ማዕከል ተደግፈዋል ያሉት አቶ አሰግድ መብራቱ ማዕከሎቹ በጋራ ከ1.39 ቢሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስትመንትን በማሰባሰብ 812 ሚሊዮን ዶላር ከኢትዮጵያ መንግሥት፣ 352 ሚሊዮን ዶላር ከዋና ዋና የልማት አጋሮች እንደ AfDB፣ EU፣ AICS፣ UNIDO፣ BMZ እና FAO እንዲሁም ከግል ባለሀብቶች 227 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጋቸውን አስረድተዋል ።
በተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪያል ፓርኮች ውስጥ እስከዚህ አመት ድረስ 122 የኢንቨስትመንት ስምምነቶች መፈረማቸውን፣ 29 ፋብሪካዎች በመቋቋም ላይ መሆናቸውን እና 14ቱ ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ በመገባት ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
አቮካዶ፣ አኩሪ አተር፣ ወተት፣ በቆሎ፣ ጥቁር አዝሙድ እና ማርን ጨምሮ የተለያዩ ምርቶችን የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በማዘጋጀት ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪያል ፓርኮች ውጥን የልማት ፕሮጀክት ብቻ አይደለም ሁሉን አቀፍ እድገትን፣ የገጠር ትራንስፎርሜሽን እና ዘላቂ ብልጽግናን ለማምጣት ብሔራዊ ቁርጠኝነት ነው ያሉት አቶ አሰግድ መብራቱ በአሁኑ ጊዜ ከ236,450 በላይ አነስተኛ አርሶ አደሮች እና 105 የህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒየኖች በተዋቀሩ ኮንትራቶች እና በተደራጀ የአቅርቦት ሰንሰለት ከፓርኮቹ ጋር መገናኘታቸውን አስረድተዋል ።
በፓርኩ ውስጥ ያሉ ካምፓኒዎች የወጪ ንግድ ገቢ 50.5 ሚሊየን ዶላር የደረሰ ሲሆን፥ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡትን የመተካት ስራዎች ደግሞ ወደ 2 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ማዳን መቻላቸውን ጠቁመዋል ።