አምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ የሚጣሉ ተጨማሪ ክፍያዎች ኢንዱስትሪዎቹ በሀገር ውስጥም ሆነ በወጪ ምርት ስራዎች ላይ ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ አያደረጋቸው ነው / አቶ መላኩ አለበል/

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሸገር ፣ ቢሾፍቱ፣ አዳማ እና ደብረ ብርሀን ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች እና ተወካዮች በተገኙበት በአምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ የሚጣሉ ተጨማሪ ክፍያዎች መነሻና ነባራዊ ሁኔታን መሰረት ያረገ የዳሰሳ ጥናት ቀረበ፡፡

የአምራች ኢንዱስትሪው የኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር እንዲያደርግ በ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ እና በሀገር በቀል ሪፎርም ፕሮግራም ተቀምጦ እየተሰራ ይገኛል፡፡

የአምራች ኢንዱስትሪውን ሀገራዊ ግቦች ለማሳካት በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በአምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ ምክንያታዊ ያልሆኑ ወይም ምክንያቱ በግልጽ ያልታወቀ ተጨማሪ ክፍያዎች ጥናት ተደርጎባቸው መፍትሔ እንደሚያስፈልጋቸው የገለጹት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል አምራች ኢንዱስትሪዎች ተወዳዳሪና ምርታማ እንዳይሆኑ ከሚያደርጓቸው መካከል የጫኝ እና አውራጅ፣ በቅርብ እርቀት የሚከፈለው የኮቴ ክፍያ እና ሌሎችንም አንስተዋል፡፡

ሚኒስትሩ አያይዘውም የእነዚህ ተጨማሪ ክፍያዎች በኢንዱስትሪዎች ላይ ከሚያሳድሩት ጫናዎች መካከል የምርታቸውን ወጪ ሲጨምር በምርት ላይ የሚኖር የዋጋ ጭማሪ፣ የኢንዱስትሪዎች ተወዳዳሪነት መቀነስ፣ የስራ ዕድል ፈጠራ እና ሌሎችንም ገልጸዋል፡፡

አክለውም በከተማና ከተማ አስተዳደር ለኢንዱስትሪዎች የተሰጠው ትኩረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸው ኢንዱስትሪዎች በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ያላቸው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ የፌደራል ፣የክልልና ከተማ አስተዳደር አመራሮች በቅንጅት መስራት ይጠበቃልም ብለዋል፡፡

በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩት ከፍተኛ አመራሮች በበኩላቸው በአምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ የሚጣሉ ህጋዊነት የሌላቸው ከፍያዎችን በተመለከተ ለውጦች መኖራቸውን እና ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆኑን ገልጸው በቀጣይም በጋራ እንደሚሰሩ አብራርተዋል።

Share this Post