የአዳዲስ አነስተኛና መካከለኛ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎችን ወደ 7,105 ለማሳደግ ታቅዶ እየተሰራ ነው፡፡

ነሐሴ 15፣ 2018 ዓ.ም (ኢ.ሚ) የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የአምራች ኢንዱስትሪውን ተወዳዳሪነት፣ ምርታማነትና ጥራት በማሳደግ የኢንዱስትሪውን የኢኮኖሚ አስተዋጽኦ ለማጠናከር ለ2019 በጀት ዓመት የተለያዩ ዋና ዋና ግቦችን አስቀምጧል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከክልልና ከተማ አስተዳደር የኢንዱስትሪ ቢሮዎች ጋር በቢሾፍቱ ከተማ ባካሄደው የሥራ ግምገማ መድረክ፣ የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸሙን ገምግሞ የ2019 በጀት ዓመት ዕቅዱ ላይ በመወያየት የጋራ አድርጓል።

በዕቅዱ መሠረት የአምራች ኢንዱስትሪውን የውጭ ምንዛሬ ገቢ በ2018 ከነበረበት 484.041 ሚሊዮን ዶላር በ2019 በጀት ዓመት ወደ 600 ሚሊዮን ዶላር ለማሳደግ እና የአምራች ኢንዱስትሪዎች አማካይ የማምረት አቅም አጠቃቀምን በ2018 ዓ.ም ከነበረበት 69.3 በመቶ ወደ 74 በመቶ ለማድረስ ግብ ተይዟል።

የሀገር ውስጥ ምርት የገበያ ድርሻን ወደ 49 በመቶ ማሳደግም ከተቀመጡት ዋና ዋና ግቦች መካከል ሲሆን፣ ይህም የአገር ውስጥ ምርቶችን በጥራት፣ በዓይነትና በተወዳዳሪነት በማሳደግ የውጭ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት የሚያግዝ አቅጣጫ እንደሆነ ተገልጿል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በ2019 በጀት ዓመት 494,805 አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር ዕቅድ ይዞ፣ የአዳዲስ አነስተኛና መካከለኛ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎችን ቁጥር በ2018 ከነበረበት 4,233 ወደ 7,105 ለማሳደግ አቅዷል።

የተቀመጡትን ግቦች ለማሳካትም የነባር አምራቾችን ምርትና ምርታማነት በማሻሻል፣ ጥራት ያላቸውን አዳዲስ ባለሀብቶች ለመሳብ፣ ለውጭ ገበያ የሚያበቁ ምርቶችን በጥራትና በዓይነት ለማምረት እንደሚሰራ ተገልጿል።

በተጨማሪም የኢንዱስትሪ ፖሊሲና ስትራቴጂዎችን በጥልቀት ወደ ተግባር ማስገባት፣ የግብዓት አቅርቦት ችግሮችን መፍታት፣ ከዩኒቨርሲቲዎችና ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጋር ትስስር መፍጠር፣ እንዲሁም የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግርን ማጠናከር በበጀት ዓመቱ ትኩረት የሚሰጣቸው የሥራ አቅጣጫዎች መሆናቸው ተጠቁሟል።

የአምራች ኢንዱስትሪ ክላስተር ማዕከላትን በክልሎች ማስፋፋትና የማበረታቻ ሥርዓት መዘርጋትም ዕቅዱን ለማሳካት ከሚወሰዱ ተግባራት መካከል ተጠቅሰዋል።

ተቋሙ የኢንዱስትሪ ልማቱ ከዘላቂና አረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ጋር የተጣጣመ እንዲሆን በማድረግ፣ የአምራች ዘርፉን የረጅም ጊዜ ዕድገት ለማረጋገጥ እንደሚሰራም ተጠቁሟል።

በተለይም የዘይት ፋብሪካዎችን የማምረት አቅም ከ2018 ዓ.ም አፈጻጸም በላይ ለማሳደግ ትኩረት እንደሚሰጥ ተመላክቷል።

በአጠቃላይ የ2019 በጀት ዓመት ዕቅዱ የአምራች ኢንዱስትሪውን ምርታማነትና ተወዳዳሪነት በማሳደግ፣ የውጭ ምንዛሬ ገቢን በማስፋት፣ የሥራ ዕድልን በመፍጠርና አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን በማቋቋም የሀገሪቱን የኢንዱስትሪ ልማት ለማፋጠን ያለመ መሆኑ ተገልጿል ።

Share this Post