ሕዝብን እና ሀገርን ለሚደጉሙ ኢንደስትሪዎች ድጋፉ ይቀጥላል

ህዳር 10/2015 ዓ.ም አዲስ አበባ (ኢ.ሚ) ሕዝብን እና ሀገርን ለሚደጉሙ ኢንዱስትሪዎች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል / የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል /

አዲስ አበባ፡ ሕዳር 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በላያ ኢንዱስትሪያል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጭ በሱሉልታ ከተማ የውኃ ፋብሪካ አስመርቆ ወደ ሥራ አስገብቷል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል እንደገለጹት ስፖርት ውኃ በቴክኖሎጂ የዳበረና ፈጥኖ ወደ ሥራ መግባት የቻለ ፋብሪካ ነው ብለዋል።

ውኃ ወለድ በሽታ በዓለማችን ያለው ተጽዕኖ ቀላል አይደለም ያሉት ሚኒስትሩ ፋብሪካው ይህን ከመቀነስ ባሻገር በምጣኔ ሀብትና በማህበረሰብ ድጋፍም ሚናው የበዛ ነው፤ ከዚህ በላይም ኃላፊነቱን እየተወጣ የሚጠናከር መሆን አለበት ሲሉ ተናግረዋል።

ፋብሪካው በተለይ ወደ ውጭ የመላክ ዓላማን ጭምር የያዘ በመሆኑ ፋይዳው የጎላ እንደሆነ አስገንዝበው ሌሎችንም የለስላሳ መጠጦችን በማምረት ለገበያ ማቅረቡ ደግሞ ሀገራዊ ጠቀሜታውን ከፍ ያደርገዋል ብለዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በውኃ ምርትና ሂደት ላይ ባደረገው ምርምርና የማሻሻያ ጥናት በተለይ አስፈላጊነታቸው አናሳ የሆኑ ከውጭ ይገቡ የነበሩ ግብዓቶችን በማስቀረት ትልቅ ሥራ እየሠራ እንዳለም ገልጸዋል።

ሌሎች የውጭ ምንዛሬን የሚያስቀሩ ጥናቶች እየተካሄዱ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ አሁን ልክ እንደ በላያ ኢንደስትሪያል ፈጣን፣ማኅበረሰቡን እና ሀገርን የሚደጉሙ ተግባራትን ለሚሰሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

Share this Post