የተቋማት ትስስርና ቅንጅታዊ አሰራር ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ወሳኝነት አለው /የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል /
ህዳር 9/2015 ዓ.ም አዲስ አበባ (ኢ.ሚ) የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢትየጵያ ታምርት ሀገራዊ ንቅናቄ ያለበትን ደረጃ ለመገምገም ፣ ቅንጅታዊ አሰራርን ለማጠናከርና የቀጣይ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ውይይት እያካሄደ ነው፡፡
በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፉን ለማሳደግ ፣በዘርፉ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ የተቀናጀ የአሰራር ስርዓት ለመዘርጋት ታስቦ የኢትየጵያ ታምርት ሀገራዊ ንቅናቄ መጀመሩን የገለጹት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ሀገራዊ ንቅናቄው ከተጀመረ አጭር ጊዜ ያስቆጠረ ቢሆንም አዳዲስ ኢንቨትመንት በመሳብ፣ የመሰረተ ልማትና የመሬት ጥያቄዎችን በመመለስ፣ የተዘጉ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ በማስገባት እና ለዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ረገድ አበረታች ውጤቶች የተመዘገቡበት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
እንደ ሀገር በግብርና፣በቱሪዝም በማዕድን እና ኢንፎርሜስን ቴክኖሎጂ ዘርፎች በርካታ ምቹ ሁኔታዎች አሉ ያሉት አቶ መላኩ በተለይም ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ በግብአትነት የሚውሉ በርካታ አቅሞች ያሉ ቢሆንም እንዚህን በቅንጅት በመምራት ረገድ ክፍተት እንዳለ ገልጸዋል፡፡
ችግሮቹን ለመቅረፍ ከፌደራል እስከ ክልልና ከተማ አስተዳደር እንዲሁም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅታዊ አሰራር ስርዓት መዘርጋት ወሳኝነት አለው ብለዋል፡፡
በዘርፉ ኢኮኖሚያዊ መዋቀራዊ ሽግግር ማምጣት፣ የዜጎችን ገቢ ማሳደግ፣ ለዜጎች የስራ እድል መፍጠር እና ተወዳዳሪነት ከፍ ማድረግ ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም ያሉት አቶ መላኩ አዳዲስ አሰራሮች፣ ሀሳቦችና አካሄዶችን ተግባራዊ ማድረግ ካልተቻለ የኢትየጵያን ህዳሴና ብልጽግና ማረጋገጥ እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡
በዘርፉ ያሉ ችግሮች እና ለመፍታት የሚያስችሉ የመፍትሄ ሀሳቦች በውይይቱ ቀርበዋል ፡፡