አላይድ ኬሚካልስ ከማምረቻ መሬት ጋር አጋጥሞት የነበረው ችግር መፈታቱ ተገለጸ

አላይድ ኬሚካልስ በአዳማ ከተማ ለረዥም ግዜ አጋጥሞት የነበረውን የመሬት የማስፋፊያ ጥያቄ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት ችግሩ እንዲፈታ መደረጉን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ ገልጸዋል፡፡

ድርጅቱ ለሳሙና እና ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ግብአትነት የሚውሉ የኬሚካል ጥሬ እቃዎችን በማምረት ሂደት ላይ የተሰማራ ሲሆን በአዳማ ከተማ ለሚያስገነባው ማስፋፊያ ፕሮጀክት አጋጥሞት የነበረው የመሬት ችግር ከአዳማ ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤት እና ከሚመለከታቸው ባላድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር ችግሩን መቅረፍ ተችሏል ብለዋል ፡፡

10 ሺህ ካሬ ሜትር ለፕሮጀክት ማስፋፊያ መሬት የተሰጠው ይህ ድርጅት ለዜጎች ተጨማሪ የስራ ዕድል በመፍጠር፣ ገቢ ምርቶችን በመተካት እንዲሁም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው ለሌሎች ፋብሪካዎች ግብአትነት የሚውሉትን ላብሳ (LABSA) እና ኢ.ኤስ.ኤል.ኤስ (ESLS) ማስፋፊያ ፕሮጀክት በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ወደ ምርት እንዲገባ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በጀመረው የኢትዮጵያ ታምርት ሀገራዊ ንቅናቄ መሠረት አምራች ኢንዱስትሪዎች እያጋጠማቸው ያሉ ችግሮችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት የመፍታቱ ሂደት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ሚኒስትር ዴኤታው አክለዋል ፡፡

#ኢትዮጵያ_ታምርት

Share this Post