ለአምራች ኢንዱስትሪው የሚያስፈልጉ የግብርና ምርቶች ጥራት ፣መጠንና ዋጋ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ተካሄደ

ህዳር/2015 ዓ.ም(ኢሚ) የግብዓት አቅርቦት ጥራትና የገበያ ትስስር ለኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግሩ ሚናቸው የላቀ ቢሆንም ለአምራች ኢንዱስትሪው የሚያስፈልጉ የግብርና ምርቶች በሚፈለገው ጥራት መጠንና ዋጋ ማቅረብ ላይ ባሉ ውስንነቶች ከዘርፉ እየተገኘ ያለው የኢኮኖሚ ጥቅም አነስተኛ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀሰን ሙሃመድ ገልፀዋል ።

በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ መሰረት ላለፉት አራት ተከታታይ ዓመታት አበረታች የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ መቻሉን ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚገጥማቸውን የግብዓት አቅርቦት እጥረት እና የጥራት ችግሮች በመቅረፍ የዘርፉን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ሀገር አቀፍ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በማስጀመር በርካታ ተስፋ ሰጭ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሩ ለኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግሩ በግብዓት አቅራቢዎች እና በአምራች ኢንዱስትሪዎች መካከል የገበያ ትስስር መፍጠር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ የተጣለበትን ሀገራዊ የኢኮኖሚ ድርሻ ማሳካት ይችል ዘንድ የግብዓት አቅርቦት እጥረት እና የጥራት ችግሮችን በመለየት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻውን የስራ ኃላፊነት እንዲወጡ ለማድረግና ቅንጅታዊ አሰራርን ለመፍጠር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያካሄደ ነው፡፡

Share this Post