ለአምራች ኢንዱስትሪ ልማት እድገትና ተወዳዳሪነት የጥናትና ምርምር ስራዎች ወሳኝነት አላቸው /አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ/

ጥቅምት 25/2015ዓ.ም አዲስ አበባ (ኢ.ሚ) በዘርፉ የተሰሩ ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ወደ ተግባራ ለማስገባት የሚረዳ የግምገማ እና የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡

የውይይቱ ዋና ዓላማ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ላይ የተሰሩ ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ሃሳቦችን ገምግሞ ወደ ተግባር በማስገባት፣ የአምራች ኢንዱስሪውን እድገት፣ ልማት እና ተወዳዳሪነት ለማረጋገጥ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

መንግስት በቀጣይ አስር አመታት ጠንካራ ኢኮኖሚ ያላት፣ለዜጎችዋ ምቹ የሆነች፣ በ2022 ዓ.ም የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት የሆነች ኢትዮጵያን የማየት ራዕይን አስቀምጦ በርካታ ውጤቶችን እያስመዘገበ ይገኛል ያሉት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ መንግስት ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ላይ ትኩረት ሰቶ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለማሳደግ ካሉ አስቻይ ሁኔታዎች መካከል ለዘርፉ ግብዓት የሚሆኑ ግብዓቶች መኖር፣ ለአለም ገበያ ምቹ የሆነ መልካምድራዊ አቀማመጥ ለአብነት ይነሳሉ ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ይህንን አስቻይ ሁኔታ በመጠቀም ዘርፉን ማዘመንና ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግሩን ማሳካት ይገባል ብለዋል፡፡

የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ሰፊ የስራ እድል መፍጠር የሚችል ነው ያሉት አቶ ታረቀኝ የዘርፉን ተወደዳሪነት ለማሳደግ የጥናትና ምርምር ስራዎች ወሳኝ በመሆናቸው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣የምርምር ማዕከላት ፣ ምሁራን እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

በውይይቱ መድረኩም 20 የጨርቃጨርቅና አልባሣት፣ 12 የቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ 11 የምግብና መጠጥ ፣ 7 የአምራች ኢንዱስትሪ፣ 11 የካይዘን በድምሩ 78 የጥራትና ምርምር መነሻ ሃሳቦች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል፡፡ በውይይት እና በግምገማ መድረኩ የሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች፣ የዩኒቨርስቲ ፕሬዘዳንቶች፣የጥናትና ምርምር ማዕከላት፣በኢንዱስትሪ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች እና የሚመለከታቸው አካላት ተሳታፊዎች ናቸው፡፡

Share this Post