ነጭ የውኃ የፕላስቲክ ጠርሙስ ለጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ግብዓትነት

ጥቅምት 24/2015 ዓ.ም (ኢሚ) የታሸጉ ውኃ አምራቾች በተለምዶ ሲጠቀሙበት የነበረውን የውኃ ማሸጊያ ፕላስቲክ ጠርሙስ ማቅለሚያ (ማስተርባች)የውጭ ምንዛሬን የሚያባክን፣ መልሶ ጥቅም ላይ የማይውል፣ የአካባቢ ብክለትን የሚያባብስና የማምረቻ ወጪን የሚጨምር ከጥቅምት 1/2015ዓ.ም ጀምሮ ጥቅም ላይ እንዳይውል መወሰኑ ይታወቃል፡፡

የውኃ ማሸጊያ ፕላስቲክ ጠርሙስ ከሰማያዊ ወደ ነጭ ቀለም መቀየሩ ሀገራችን ለማቅለሚያ ጥሬ እቃው በዓመት ታወጣ የነበረውን ከ50 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ የውጭ ምንዛሬ ማዳን እንደሚቻል የኢትዮጵያ በቨሬጅስ አምራች ኢንዱስትሪዎች ማህበር ቦርድ ፕሬዘዳንት ጌትነት በላይ (ኢንጂነር) ገልጸዋል፡፡

ፕሬዘዳንቱ አክለውም የውኃ የፕላስቲክ ጠርሙስ ነጭ መሆኑ ለጨርቃጨርቅ ማምረቻ ግብዓት የሚሆን ፓሊስተር፣ፋብሪክና ያርን በሰፊው በማምረት ከውጭ የሚመጣውን ሀገር ውስጥ በመተካት በዓመት ውስጥ ከ45-50ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማዳን ያስችላል ብለዋል፡፡

ነጭ የፕላስቲክ ጠርሙሱ ተፈጭቶና ፕሮሰስ ተደርጎ ወደ ውጭ ኤክስፖርት ሲደረግ ቀድሞ ከነበረው(ማስተርባች) በዓመት ውስጥ በአማካይ በአንድ ቶን እስከ 15 የአሜሪካን ዶላር ተጨማሪ ገቢ እንደሚያስገኝ ኢንጅነር ጌትነት ገልፀዋል፡፡

አከፋፋዎች፣ቸርቻሪዎችና ባለሱቆች ያለ ማስተርባች የተመረተ ነጭ ፕላስቲክ ጠርሙስ የታሸገ ውኃ ለህብረተሰቡ ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበው የውሳኔውን ተፈፃሚነት የኢፌዴሪ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣንና የክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የአካባቢ ጥበቃ ቢሮ የመቆጣጠር ኃለፊነት እንደተሰጣቸው ጠቁመዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ም/ዳይሬክተር አቶ ስለሽ ለማ በበኩላቸው ሁሉም ሰው በነጭ የፕላስቲክ ጠርሙስ የተመረተ ውኃን በመጠቀም ለአካባቢ ጥበቃና ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ አሳስበዋል፡

Share this Post