የሁለትዮሽ ኢኮኖሚያዊ ትስስርን የሚያጠናክር ውይይት ተካሄደ

ጥቅምት 21/2015ዓ.ም አዲስ አበባ(ኢ.ሚ) የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀሰን ሙሃመድ በካሜሮን የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዘዳንት ኡጌኒ ፍራንሲስ የተመራ ልዑክ በቢሯቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

ውይይቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊ ትስስር ማጠናከር ላይ ትኩረቱን ያደረገ ሲሆን እንደ ሀገር እየተተገበረ ስላለው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፕሮግራም ፣ በሀገር ውስጥ ስላሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችና ምቹ ሁኔታዎች ፣ መንግስት ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ እያደረገ ያለውን የድጋፍ ማበረታቻዎች በተመለከተ ውጤታማ ውይይት ተድርጓል፡፡

አምራች ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ ከተወሰዱ አማራጮች መካከልም በ2021 ከተሰጡ የብድር አቅርቦት ውስጥ 70 በመቶ ለግሉ ዘርፍ እንደተሰጠ እና ይህም ለአምራች ኢንዱስትሪ እንደ መልካም አጋጣሚ መሆኑን ለአብነት የተነሳ ሲሆን በርካታ የመንግስት ልማት ድርጅቶች ወደ ግል ይዞታ የማዞር ስራም ሌላው እንደ አብነት ከተወሰዱ የድጋፍና ማበረታቻዎች ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ ያሉ መልካም ተሞክሮዎች ወደ ካሜሮን የሚሸጋገሩበት፣ የካሜሮን ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው መዋለ ንዋያቸውን ስራ ላይ የሚያውሉበት የኢንዱስትሪ አማራጮችን ለማመላከት፣ የተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎች እና ድጋፎችን ተመርኩዘው ኢንቨስት ማድረግ የሚችሉበት ሁኔታ እንዳለ በውይይቱ ተገልጿል፡፡

ካሜሮን የሁለቱን አገራት ትስስር ለማጠናከር የካሜሮንን-ኢትዮጵያ የወዳጅነት ግሩፕ በሚል በፓርላማ ደረጃ የተፈጠረ አደረጃጀት እንዳለ የተገለጸ ሲሆን በቀጣይም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ፣ኢንቨስትመንትና ዲፕሎማሲ ግንኙነቶችን ለማጠናከር በሁለቱም ወገኖች በኩል በርካታ ስራዎች እንደሚሰራ ተጠቁሟል፡፡

Share this Post