ኢትዮጵያ በጨርቃጨርቅና አልባሳት ፋሽን ኢንዱስትሪ የአፍሪካ መናኸሪያ እንድትሆን እየተሰራ ነው፡፡

ጥቅምት 10/2015 ዓ.ም አዲስ አበባ (ኢ.ሚ) ኢትዮጵያ በጨርቃጨርቅና አልባሳት ፋሽን ኢንዱስትሪ የአፍሪካ መናኸሪያ እንድትሆን ከሚያስችሉ ስራዎች አንዱና ዋናው የአምራች ኢንዱስትሪ ፖሊሲ መሻሻል ሲሆን ለዚህ ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ የአምራች ኢንዱስትሪ ፖሊሲን በማሻሻል በትኩረት እየሰራ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀሰን መሃመድ ተናግረዋል፡፡

መንግስት የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪው ፈጣን እድገት እንዲያስመዘግብና ዘርፉ ለማሳደግ የተለያዩ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በማውጣት ምቹ የኢንቨስትመንት አካባቢ የሚፈጥሩ ፣ በዘርፍ የተሰማሩትን ባለሀብቶችና ባለሙያዎች የሚያበረታቱ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል፡፡

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለፃ በኢትዮጵያ የጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ እየታየ ያለው ለውጥ በክህሎትና አቅም የተገነቡ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች እንዲሳቡ አድርጓቸዋል።

የጨርቃጨርቅ ዘርፉ ከትናንሽ እስከ ከፍተኛ ጨርቃጨርቅ ማምረቻ ኩባንያዎች ድረስ ለሰፊ የሥራ ዕድል ፈጠራ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ ሲሆን በተለይም ሴቶች በዚህ ኢንዱስትሪ ውስጥ በብዛት የተሰማሩ እና በስራ እድል ፈጠራ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው አስረድተዋል።

12ኛው ሃብ ኦፍ አፍሪካ የፋሽን ሳምንት በሃያት ሬጀንሲ ሆቴል በትላትናው ዕለት በይፋ የተከፈተ ሲሆን የፋሽን ሳምንቱ ለተከታታይ አምስት ቀናት የሚቆይ ይሆናል፡፡

Share this Post