በምግብ ሉአላዊነት ዘርፍ የዘይት ፍላጎትን በሀገር ውስጥ ምርት በመሸፈን አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር ያስፈልጋል ( አቶ መላኩ አለበል )
ነሐሴ 14/2018 ዓ.ም (ኢሚ) የኢፌዴሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የምግብ ዘይት አምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅማቸውን ለማሳደግ፣ እየገጠሟቸው ያሉ ተግዳሮቶች እና የመፍትሔ ሃሳብ ላይ ያተኮረ ውይይት አካሄደ፡፡
የውይይቱ ዓላማ በዘርፉ ባሉ ዕድሎችና ተግዳሮቶች ላይ ተወያይቶ ዘላቂ የመፍትሄ ሃሳብ ማስቀመጥ ነው፡፡
በውይይቱ የ2018 የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ መሪ ቃል “ኢትዮጵያ ታምርት ለሁለንተናዊ ሉአላዊነት” እንደነበር በማስታወስ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል መሪ ቃሉ የተመረጠበት ዋና ምክንያት ኢትዮጵያ የምታመርተው የሉአላዊነት ጥያቄዋን ለመመለስና አጠቃላይ ሀገራዊ ክብርን የሚያስጠብቁ ስራዎችን ታሳቢ በማድረግ ነው፤ ከዚህ ውስጥ አንዱ የምግብ ሉአላዊነት ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡
በምግብ ሉአላዊነት ዘርፍ የዘይት ፍላጎትን በሀገር ውስጥ ምርት በመሸፈን ወደ ውጪ ለመላክ ማቀድ፣ ተግዳሮቶችን መፍታት እና አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል።
82 በመቶ የሚሆነውን የሀገር ውስጥ የምግብ ዘይት ፍላጎት ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት እንደሚሸፈንና ሉአላዊነታችንን እየተገዳደረ ያለ ጉዳይ ነው ያሉት አቶ መላኩ በመሰረታዊ ጉዳዮች ማለትም በግብሃት፣ በአቅርቦት፣ በፖሊሲ ፣በማምረት አቅም እና ለምርትና ምርታማነት ማነቆ በሆኑ ጉዳዮች፣ የመፍትሄ ሃሳቦች እና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ መወያየት ያስፈልጋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
እንደ ሀገር 41 በላይ በምግብ ዘይት አምራችነት የተሰማሩ ከፍተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች አሉ ያሉት አቶ መላኩ በተለይም 21 ከለውጡ አመታት ወዲህ የተቋቋሙና ዕድገታቸው በቁጥር ብቻ ሳይሆን ከአጠቃላይ ምርት 63 በመቶ የሚሆነው በእነዚህ አምራች ኢንዱስትሪዎች እንደሚመረትም አክለዋል፡፡
የሀገር ውስጥ የምግብ ዘይት ፍላጎትን በመሸፈን ረገድ ከፍተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ያላቸው ሚና በተመለከተ በ2012 እና 2013 ከነበረው የአምስት በመቶ ድርሻ ወደ 18 በመቶ መድረሱን እና የማምረት አቅማቸው 53 በመቶ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ የእነዚህን አምራች ድርጅቶች የማምረት አቅም በማሳደግ የሀገር ውስጥ ፍላጎት በሀገር ውስጥ ምርት እንዲሸፍን ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
ለውይይቱ መነሻነትም የምግብ አምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም አጠቃቀም፣ እንደ ሀገር ያላቸው ሚና፣ እንደ ሀገር የምርት ፍላጎትና አቅርቦት፣ በዘርፉ እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶችና መፍትሄ ሃሳብ የያዘ ጥናት ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡
በውይይቱ የኢፌዴሪ ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ፣ገንዘብ ሚኒሰቴር፣ ገቢዎች ሚኒስቴር፣ ግብርና ሚኒስቴር ፣ጉምሩክ ኮሚሽን፣ ብሔራዊ ባንክ ፣ንግድ ባንክ ፣በምግብ ዘይት አምራችነት የተሰማሩ ድርጅቶች እንዲሁም የምግብ ዘይት አምራች ኢንዱትሪዎች ማህበር ተሳታፊ ሆነዋል፡፡